እንኳን ወደ አንድነት ፓርክ በደህና መጡ

የአንድነት ፓርክ በጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የግንባታና የማደራጀት ሥራው በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ መስከረም 29፤ 2012 ዓ.ም ታላላቅ የሃገር መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት የተደረገ የቱሪስት መስህብ ነው፡፡ የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በውስጡም ልዩ ልዩ የታሪክ፣የተፈጥሮ እና የባሕል መስህቦችን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ የአንድነት ፓርክ የሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት የተቆረቆረው በ1878 ዓ.ም. ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሳይጨምር የሰባት መሪዎች የሥራና የመኖሪያ ቦታ በመሆን አገልግሏል፡፡ ቤተ መንግሥቱ 40 ሄክታር ሥፋት ያለው ሲሆን ከዳግማዊ ዐጼ ምኒሊክ ዘመን ጀምሮ የተገነቡ ልዩ ልዩ ሕንጻዎችንና በእጽዋት የተሞላ ሰፊ ሥፍራን ይዟል፡፡

አሥሩ መስህቦች

ይህ ቦታ ጎብኚዎች በእግር ጉዞ ወይም በጉዞ አጋዥ መሳሪያዎች የሚንሸራሸሩበት እና ከከፍታማ ዙሪያ ገባውን የሚቃኙበት ነው፡፡የአዲስ አበባ ከተማን ከፊል ገጽታ ቁልቁል ለመመልከት ምቹ የሆነ ነው፡፡ ይህ አረንጓዴ ሥፍራ አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ ከ6000 መኪና ጭነት በላይ አፈር ተጓጉዞ ተደልድሏል፡፡ በአረንጓዴ ስፍራው ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ መስህቦች፤ አገራዊ ሀብቶቻችንን እና መገለጫዎቻችንን የሚያንጸባርቁ የጥበብ ሥራዎች ተካተዋል፡፡

የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት በአንድነት ፓርክ ከሚገኙ ሁለት መካነ-እንስሳት ውስጥ አንዱ ሲሆን በ2011 ዓ.ም የተገነባ ነው፡፡ ይህ ስፍራ የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት ተብሎ የተሰየመው በሃገራችን ብቻ ከሚገኘው ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በመነሳት ነው፡፡ ይህ ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ዴዴሳ እና አልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ በዋነኛነት የሚገኝ ነው፡፡ ይህ መካነ እንስሳት ከአንበሶች በተጨማሪ የደጋ አጋዘኖች (ኒያላ) እና የአባኮዳ አውደ ርዕይን ያቀፈ ነው። በዚህ መካነ-እንስሳት ርዝመቱ 175 ሜትር የሚሆን ሰው ሰራሽ ዋሻ የሚገኝ ሲሆን፤ ዋሻው በሃገራችን ባለሙያዎች ከብረት፣ ሲሚንቶ፣ ፋይበር እና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶች የተገነባ ነው። ይህ ዋሻ የሶፍ ዑመር ዋሻ ገፅታን እንዲላበስ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፤ ስፍራው ተፈጥሯዊ ገፅታ እንዲኖረውም የተለያዩ እንስሳት ድምፅን የሚያሰሙ የድምጽ ግብአቶች፣ ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎች፣ ኩሬዎች እና አነስተኛ ድልድይን እንዲያቅፍም ተድርጓል። ጎብኚዎች ውስጥ-ለውስጥ በዚህ ዋሻ ውስጥ በመንቀሳቀስ ለእይታ ተብለው በተዘጋጁ ሰፋፊ የመስታወት መስኮቶች ውስጥ የእንስሳቱን እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ፡፡ በሌላ በኩል እንስሳቱ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሆኖ በተዘጋጀላቸው ሰፊ ስፍራ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በተጨማሪም ይህ ስፍራ ለእንስሳቱ ማደሪያ፤ ምግብ ማቀነባበሪያ እና ህክምና መስጫን በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡

የአገር በቀል እፅዋት ማሳያ በውስጡ የተለያዩ አገር በቀል እፅዋትን እና የግንባታ ዘዴዎችን ለጎብኚዎች የሚያሳይ የጉብኝት ማዕከል ነው። በዚህ ስፍራ ውስጥ በዋነኝነት ለመድሃኒትነት፣ ለውበት፣ ለቅመማ ቅመምነት፣ ለምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ ለእንጨት ስራ እና ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ሃገር በቀል እፅዋት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የገጠሩን አኗኗር፣ የቤት አሠራር ጥበብና ስነ-ምድራዊ ገፅታ ማራኪ በሆነ መንገድ ለጎብኚዎች ያቀርባል፡፡ በሌላ መልኩ በዚህ ስፍራ በሁለት ግመሎች እና በኤሊ ቅርፅ የተሰሩ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግቢው ውስጥ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ እና አርጅተው ከወደቁ ዛፎች የተሰሩ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች የስፍራው ድምቀቶች ናቸው፡፡ የሃገር በቀል እፅዋት ማሳያ ስፍራን ከሌሎች መስህቦች ለየት የሚያደርገው ሙሉ በሙሉ በሰው እጅ ያለ ማሽን እገዛ የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተሰበሰቡ የእፅዋት፣ የካብ፣ የድንጋይ ስራ፣ የባህላዊ ቤት ግንባታ እና ሌሎች ሙያተኞች የተሳተፉበት ነው፡፡

የዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ቤተ-መንግስት እልፍኞች ግንባታ የተጀመረው በ1880ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ ስብስቡ በተለምዶ እንቁላል ቤት ተብሎ የሚታወቀውን ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ ጨምሮ በመተላለፊያ ሠገነት ተያይዘው የተሠሩት ቤቶች የዐጼ ምኒልክ መኝታ ቤትና እልፍኝ፣ የእቴጌ ጣይቱ መኝታ ቤትና እልፍኝ፣ የእልፍኝ አዳራሽን እና የልዑላን መኝታ ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡ በጣራው ቅርጽ ምክንያት እንቁላል ቤት ተብሎ የሚታወቀው ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ የዳግማዊ ምኒልክ ጸሎት ቤት፣የቅኝት ሠገነት እና ጽ/ቤት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ እንዲሁም በጸሎት ቤቱ መግቢያ አካባቢ ላይ የተገጠመው የድምጽ ማስተላለፊያ ቱቦ ጸሎት ቤቱን ከጽሕፈት ቤቱ ጋር የሚያገናኝ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ስልክ የተቀመጠባቸው ሁለት ትንንሽ ክፍሎች ወደ ዐፄ ምኒልክ መኝታ ቤት በሚወስደው መተላለፊያ ኮሪደር ውስጥ በስተግራና በቀኝ ይገኛሉ፡፡ በወደ ምስራቅ አቅጣጫ ተነጥሎ የሚታየው እና የእንጨት ግድግዳ ያለው ቤት በ1923 ዓ.ም. የተገነባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሠብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን፤ በወደ ምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ የዳግማዊ ምኒሊክ እልፍኝ አቅራቢያ የሚገኘው ባለአንድ ክፍል አነስተኛ ቤት የጦር ሚኒስትሩ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) መቆያ ክፍል ነው፡፡

የአንድነት ቤተመዛግብት የሕንጻው እድሳት እና የማደራጀት ስራው ተጠናቆ ግንቦት 27፣2015 ዓ.ም ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን ከ140 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የጽሑፍ ሰነዶች የተቀመጡበት ሥፍራ ነው።ኢትዮጵያ የጽሑፍ ሥልጣኔ ካላቸው ጥቂት የዓለም አገራት አንዷ ነች። በሺህ የሚቆጠር ዕድሜ ያለው የጽሑፍ ሥልጣኔ ጥቅም ላይ ከዋለባቸው አገልግሎቶች አንዱ መንግሥታዊ የአስተዳደር ሥራ ነው፡፡ ይህን ሥራ ሲያካሂዱ ከነበሩ ተቋማት መካከል ዋነኛው የጽሕፈት ሚኒስቴር ሲሆን የአንድነት ቤተመዛግብት በአፍሪካ ብቸኛው አገር በቀል ቤተመዛግብት ነው ማለት ይቻላል። በሕንጻው የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የምናገኛቸው ሰነዶች የተደራጁት በተለያዩ መንግስታት ዘመን ሲሆን የሁሉም ሰነዶች ምንጭ ግን ታላቁ ቤተመንግሥት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአንድነት ቤተመዛግብት ውስጥ ለተከማቹት ሰነዶች በዘመናዊ መልኩ የጥበቃ፣የእንክብካቤና የማደራጀት ሥራ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ አውደ ርዕይ በአንድነት ቤተመዛግብት ውስጥ የሚገኙ ሰነዶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራን የማዘመን እንቅስቃሴ አንድ አካል ሲሆን በአውደ ርዕዩ ከ1870ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ዓ.ም. ባሉት ዘመናት የተጻፉ ሰነዶችና የድምፅና የምስል ክምችቶች በሶስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ተደራጅተው ቀርበዋል። እነዚህም የውጭ ጉዳይ፣ የአገር ውስጥ ጉዳዮች እና ሌሎች ማህበራዊና ባህላዊ ገጠመኞች ናቸው።በነዚህ ሶስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ሥር ዘጠኝ ጭብጦች ተለይተው ቀርበዋል።

ዙፋን ቤት አንድ መቶ ዓመታት ገደማ እድሜ አስቆጥሯል፡፡በዚህ ሕንፃ ላይኛው አዳራሽ የነገሥታቱ ዙፋን የሚቀመጥበት ሆኖ መሪዎቹ ከሀገር ውስጥና ከውጪ የሚመጡ እንግዶቻቸውን የሚቀበሉበት፣ የሚመክሩበት፣ የሚወስኑበት እና በጀርባው ባለው ክፍልም ግብዣ የሚያደርጉበት ነበር፡፡ ምድር ቤቱ በዘመኑ ለመጠጥ ማስቀመጫነት (ማቀዝቀዣነት) አገልግሎት ይውል ነበር፡፡የዙፋን ቤቱ ላይኛው ክፍል ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ የደርግ አባላት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ምድር ቤቱ ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ ባለስልጣናት ለሥምንት ዓመታት የታሰሩበትና በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የተለያዩ እስረኞች በየዘመኑ የታሰሩበትና የተገደሉበት ነው። በአሁኑ ወቅት የአንድነት ፓርክ ሙዝየም ዋና ዐውደ ርዕይ በዚህ ሕንጻ ውስጥ ይገኛል፡፡ ዙፋኑ የሚገኝበትን ክፍል ጨምሮ በግራ፣ በቀኝ፣በጀርባና ምድር ቤት ውስጥ ሕንጻው አምስት የዐውደ ርዕይ ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የዙፋን ክፍል፣ የእምነት፣ የአፈታሪክ፣የመንግስታት እና የአቢዮቱና የቀይ ሽብር ዐውደ ርዕዮች ናቸው።

ይህ የግብር አዳራሽ የተገነባው በዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ ዘመን በ1890-91 ዓ.ም ነው፡፡አዳራሹ በተሰራበት ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ ዘወትር ግብር ያበሉበት የነበረ ሲሆን በሂደት ግን ህዝቡ እየበረከተ ስለሄደ ግብር የማብላቱ ሥርዓት በታላላቅ ሃይማኖታዊ እና በዘውድ በዓላት ብቻ ተወስኗል፡፡ የግብር አዳራሹ በተለያዩ ዘመናት ታላላቅ ታሪካዊ ሁነቶችን አስተናግዷል፡፡በ1955 ዓ.ም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ በአዲስ አበባ የተገኙ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች መንግስታዊ እራት ተጋብዘውበታል፡፡በ1972 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) ጉባኤ ተሰናድቶበታል፡፡በቅርቡም በግንቦት 2011 ዓ.ም በ ‹‹ገበታ ለሸገር›› ዝግጅት አማካኝነት አዲስ አበባን ለማስዋብ 5 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው የእራት መስተንግዶ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ተካሂዶበታል፡፡የግብር አዳራሹ በየዘመኑ እድሳት ሲደረግለት ቆይቷል፡፡በግብር አዳራሹ ውስጥ የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዙፋን፣ከሰም የተሰራየ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ቅርፅ እና የተለያዩ የግብር እቃዎች ይገኛሉ።

ይህ ማዕከል እጽዋት ለምርምር፣ለትምህርት፣ለአካባቢ ጥበቃና ለጉብኝት በፅድቀታቸው አልያም በዘራቸው ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ታስቦ የተገነባ ነው። ማዕከሉ በመከለያ ቤት እና በመስክ በኢትዮጵያ በሚገኙ አምስቱ የስነ ምህዳሮች ማለትም በረሀ፣ ቆላ፣ ወይናደጋ፣ ደጋ እና ውርጭ የሚበቅሉ ተክሎችን አቅፎ ይገኛል። በመስክ የሚገኘው የእጽዋት ማዕከሉ ክፍል ወይናደጋን እንዲወክል ታስቦ የተገነባ ነው። መስኩን ጎብኝተው እንደ ጨረሱ 3200 ሜ2 ቦታን የሚሸፍነው የመከለያ ቤት (Green house) የሚገኝ ሲሆን ከተራራ እስከ ሸለቆ ያለውን የኢትዮጵያ የእጽዋት መስክ የሚያሳይ ስፍራ ነው። ስፍራው ሃገር በቀል እና ሃገር በቀል ያልሆኑ ከ230 በላይ የእጽዋት አይነቶችን የያዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ15 በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚበቅሉ ብርቅዬ እጽዋት ናቸው። በማዕከሉ መሬት ላይ ከበቀሉት ተክሎች በተጨማሪ ከ175 በላይ የእጽዋት አይነቶች ዘር ተቀመጦ ይገኛል። የመከለያ ቤቱ ውርጭን፣ ደጋን፣ ቆላን እና በረሃን የሚወክሉ ተክሎች የሚገኙበት ነው። የማዕከሉን የአየር ፀባይ ለማስተካከል እና የተክሎችን እርጥበት ለመጠበቅ በካፊያ መልክ ውሃ እንዲዘንብ ተደርጓል።

የአንድነት መካነ-እንስሳት 37 አጥቢ እንስሳት እና የአእዋፍ ዝርያዎችን በውስጡ አቅፎ የሚገኝ በአይነቱ በሃገራችን የመጀመሪያው መካነ-እንስሳት ነው፡፡ በመካነ-እንስሳቱ ዘጠኝ የዐውደ ርዕይ ስፍራዎች የሚገኙ ሲሆን እነሱም የሚርካት፣ የውሃ ውስጥ እንስሳት ማሳያ (አኳሪየም)፣ የፒኮክ፣ የኤሊ ማሳያ ስፍራ ፤የአቦ ሸማኔ፣ የነጭ አንበሳ፣ የተኩላ፣ የጭላዳ ዝንጀሮ፣ የአዕዋፍ እና የዚህ መካነ-እንስሳት ድምቀት የሆነው የሳፋሪ ዐውደ ርዕይ በውስጡ የተለያየ ዝርያ ያላቸው እና በዋነኛነት ሳር በል የሆኑ ማለትም (ቀጭኔ፤ኢምፓላ፤ቶራ ፈረስ፤አጋዘን፤ውድንቢ፤ሰጎን ና የሜዳአህያ ወዘተ) ዐውደ ርዕዮች ናቸው፡፡ በሃገራችን የመጀመሪያ የሆነው የውሃ ውስጥ እንስሳት ማሳያ (አኳሪየም) በአንድነት መካነ-እንስሳት የሚገኝ ሲሆን ከአስራ ሶስት በላይ የአሳ ዝርያዎችን በሶስት አይነት ኤግዚቢሽኖች ለጎብኚዎች የሚታዩበት ስፍራ ነው፡፡ ሌላው በመካነ-እንስሳቱ ውስጥ ለየት ባለ ሁኔታ የተዘጋጀው የሰው ሰራሽ የወፍ ጎጆ (Aviary) ሲሆን፤ ከትናንሽ እስከ ግዙፍ የአዕዋፍ ዝርያዎችን በጣም ማራኪ በሆነ ሁኔታ ለጎብኚዎች እንዲታይ የተዘጋጀ ነው፡፡ የዚህ መካነ-እንስሳት ሌላኛው ድምቀት የሳፋሪ አውደ ርዕይ ሲሆን በውስጡም ዘጠኝ አይነት እንስሳት የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ቶራ ፈረስ፣ የደጋ አጋዘን፣ ኢምፓላ፣ ውድንቢ፣ ሳላ፣ የቆላ አጋዘን እና ነጭ አውራሪስ ናቸው፡፡ በፓርካችን የተቋቋሙት ሁለት መካነ-እንስሳት ማለትም የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት እና የአንድነት መካነ እንስሳት የዱር እንስሳቱን ተፈጥሯዊ አካባቢ በሚመስል መንገድ ተፈጥሯዊ ገፅታን ተላብሰው የተገነቡ ናቸው፡፡

በአንድነት ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ የጉብኝት መዳረሻዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ የሚገኙ የክልሎች እልፍኞች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡እልፍኞቹ የየክልሎቹን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ መስህቦችን በጥቂቱ ለጎብኚዎች ያስተዋውቃሉ፡፡እልፍኞቹ ሥለ ክልሎቹ መሠረታዊ መረጃ በተንቀሳቃሽ ምሥል(ቪዲዮ)፣በሥነ ሥዕል እና በሌሎች የባሕል ውጤቶች በጥቂቱ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡አሠራራቸውም በዘመናዊ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የተቃኘ እና በጎብኚዎች ላይ የብሩህ ተሥፋ ሥሜት እንዲፈጥር የታሰበ ነው፡፡

ሌሎች ፓርኮቻችን

የአንድነት ፓርክ የጉብኝት ካርታ

የQR ኮድን ይቃኙ

የQR ኮድን በመቃኘት የጉብኝት ካርታውን ማውረድ ይችላሉ።

QR Code Image
Journey Map Image