አንድነት የመኪና ማቆሚያ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን ያቀፈ በከተማችን በአይነቱ ልዩ የሆነ ህንፃ ነው። ህንፃው ወደ አንድነት ፓርክ የሚገቡ ጎብኚዎች እና ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ ተቋማት ተገልጋዮች መኪናቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ ስፍራ እንዲያቆሙ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የተገነባ ነው። ይህ ፕሮጀክት በከተማችን የሚስተዋለውን ከፍተኛ የመኪና መቆሚያ ችግር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የአስፋልት ዳር የመኪና ማቆም፣ የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ የመኪና ማቆሚያ እውን ያደረገ ነው፡፡ ህንፃው በአጠቃላይ ዘጠኝ ወለሎች ያሉት ሲሆን አምስቱ የምድር ቤት ወለሎች ለመኪና ማቆሚያነት የተዘጋጁ ሲሆን በአጠቃላይ ከአንድ ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ ናቸው። ከምድር በላይ ያሉት አራት ወለሎች የተለያዩ ሱቆች፣ የምግብ እና መጠጥ በሸጫዎች፣ የአየር ትኬት ቢሮ፣ የቴሌኮም አገልግሎት ቢሮ፣ ባንኮች የተለያዩ ቢሮዎችን እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችን የያዙ ናቸው። በህንፃው በአንድ ጊዜ እስከ አራት መቶ ታዳሚዎችን ሊይዝ የሚችል አምፊቴያትር ይገኛል። ህንፃውን አስደናቂ ከሚያደርጉት በርካታ መለያዎች ውስጥ አንዱ ርዝመቱ 105 ሜትር የሆነው ወደ አንድነት ፓርክ የሚያስገባው የምድር ለምድር መተላለፊያ (ታናል) ነው። በአጠቃላይ ህንፃው በዘመናዊ የደህንነት መጠበቂያ እና የእሳት አደጋ መከላከያ ዘዴዎች የተደራጀ እና የተገልጋዮችን ምቾትና ድህንነት እንዲያስጠብቅ ታስቦ የተገነባ ነው።